አንነስ /ሠዉ እንሁን/

Poems

አንነስ አንዉረድ . . . ከሠዉነት ማማ
በሠዉነታችን . . . ከተሠጠን ግርማ
ወርደንማ አንግባ . . . ከንስሶቹ መንጋ
ሠው በመሆን ብቻ . . . ከተቸረን ጸጋ

እንኑር . . . ሥፍራችን
ከሠዉነት ጎራ . . . ከዉሃ ልካችን
እንሁን ሠዉ . . . ግዴለም
ከሠዉነት ጎድለን . . . አንዳች አናተርፍም

ከመሰይጠን ርቆ . . . መሰልጠን ለገባዉ
እንደ እንስሳ ሳይሆን . . . እንደ ሠው ለኖረው
ጨለማን የሚገፍ . . . ሠውነት ብርሃን ነው
በጎ ሠው ለኩሶት . . . ሌላዉም ሚሞቀው

በቁም ሳለን ዘርተን . . . ሞተንም ምናጭደው
የሚያሽት ቡቃያ . . . ሠዉነት ምርት ነው
የሚያተርፍ በብዙ . . . ከራሳችን አልፎ . . . ለሌሎች ምንቸረው
ከወርቅ፣ ካልማዝ ሚበልጥ . . . ሠዉነት ሃብት ነዉ

ላመኑት ባምላክ ዘንድ . . . የሚያስገኝ ሞገስን
ላላመኑት ደግሞ . . . የሚያድስ መንፈስን
ሠዉነት ኣክሊል ነው. . . መልካም ለሚያስብ ሠዉ
ሠው በመሆን ብቻ . . . ሁሌም የሚደፋዉ

አንነስ አንዉረድ . . . ከሠዉነት ማማ
በሠዉነታችን . . . ከተሠጠን ግርማ
ወርደንማ አንግባ . . . ከንስሶቹ መንጋ
ሠው በመሆን ብቻ . . . ከተቸረን ጸጋ

በሠዉነት ሚዛን . . . ሠዉ ሠዉን ሚለካዉ
ባስተሳሰብና . . . በሥነምግባር ነዉ
የሠው ደም . . . ቀይ ነው
ቆዳችንም ቆዳ   . . . ስጋም ያው ባዳ ነው

ሞት አይቀርምና  . . . ሲማስ መቃብራችን
ያፈር ሥር ኣፈር ነው . . . ሁለ ነገራችን
ግና በቁም ሳለን . . . ቀድመን የፈጸምነው
ሠዉ ሆነን  በመኖር . . . በፍቅር ያቆየነዉ
መልካም ምግባራችን . . . ምንግዜም ህያዉ ነው
ሲነገር . . . ሲወሳ . . . ሲታወስ ሚኖረዉ
ሞተንም  ሚያኖረን . . . መልካም ሥራችን ነው

ሥለዚህ . . . አንነስ . . . አንኩሰስ ግዴለም
በተሰጠን ጸጋ . . . እንግዘፍ ዘለዓለም
ታሪካችን ይለይ . . . ከእንስሳዉ ከሌላው
እንደሠው በማሰብ፣ እንደሰዉ በመኖር . . . እናድርገዉ ህያዉ

አንነስ አንዉረድ . . . ከሠዉነት ማማ
በሠዉነታችን . . . ከተሠጠን ግርማ
ወርደንማ አንግባ . . . ከንስሶቹ መንጋ
ሠው በመሆን ብቻ . . . ከተቸረን ጸጋ

ግንቦት 7 2012 ዓም
በሃብታሙ ደሃ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *