እግዜር ያደላትን የተፈጥሮ ቀለም እየተጠቀመች
ተላላው ዕድሜዬን ዘወትር እያሰላች …
ለኔው በመለፈፍ ምትሳለቅብኝ ሰላም እየነሳች …
ጎጆዬ ውስጥ ሆኜ አሻግሬ ማያት የስደት ዛፍ አለች፤
ሁሌም አያርመኝም ዘወትር አያታለሁ
“ማሽላ እያረረ …” እንዲል ያገሬ ሰው
ተደስቼ ሳይሆን በውስጤ እያነባሁ
አይቻት ስቃለሁ …፤
ይህች የስደት ዛፍ አረንጓዴነቷን ታሪክ ልታረገው
ለቢጫነት ጉዞ መወየብ ስትጀምር አጉተመትማለሁ
ከሷም፣ ከተፈጠሮ ደግሞም ከራሴ ጋር ሙግት እገጥማለሁ
ጉንጬን በመዳፌ አስደግፈውና በሃሳብ ነጉዳለሁ …፤
የተፈጥሮ ፀጋ ቀለሙዋን እያየሁ
ደግሞ ዳግም መጣ የበጋው ወቅታቸው?
… ብዬ ጠይቃለሁ
የስደት ሀገሬን ተፈጥሮ እያማረርኩ
ከሃገሬ ጋራ አነፃፅርና ራሴን አፅናናለሁ …፤
ሆኖም አይሰልቸኝ መስኮት አሻግሬ
ያችን የስደት ዛፍ ዳግም አያታልሁ
ቢጫነቷን ደግሞ ታሪክ እያረገች ወደ አረንጓዴነት መንደርደር ስትጀምር
ያው እንደልማዴ ከራሴ እጣላለሁ …፤
በዛፉዋ አሻግሬ የኔን ዕድሜ እያየሁ
እንዴት ነው ሚፈጥነው ይሄ ክረምታቸው?
እያልኩ ሳይታክተኝ ዘወትር ጠይቃለሁ …፤
ይመሻል ይነጋል … እኔም ጠይቃለሁ
ውስጤ ግን ይጨሳል በዕድሜዬ ዘልዛላው
ለሚረባ ተግባር ከምኞት ባልወጣው
ግን አንዳች ሳይፈይድ ልደት በሚያከብረው …፤
———————–// // ———————–
ሃብታሙ ደሃ
ጥር 2004 ዓ.ም. /ስዊድን/