ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ
ከምጥ ጭንቀት ፈቀቅ ባለ
ቀናት ሳምንታትን ተሻግሮ ወራት ሊያስጨንቅ የማለ
ያዳም ዘር ሊያዉቀው ሚገባ ለካስ በጽንስ ወቅት የባሰ አለ !
ተጸንሰን፣ ተወልደን አድገን ያዳም ዘር ነን ለምንለው
ከማሳደግ በዘለለ መጸነስ መዉለድ ላልቻልነው
ምናል ፈጣሪ ለሁላችን ፈቅዶልን ብንቋደሰው
የእናትነትን ስቃይ ማጣጣም ብንችል ቀምሰነው
አብሮ መታመም ቢያቅተን በማየት ብንታመመው !
ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ
ከምጥ ጭንቀት ፈቀቅ ባለ
ቀናት ሳምንታትን ተሻግሮ ወራት ሊያስጨንቅ የማለ
ያዳም ዘር ሊያዉቀው ሚገባ ለካስ በጽንስ ወቅት የባሰ አለ !
ወደዚህ ዓለም ለማምጣት ምትኳንና ምትኬን
ወደናትነት ጉዞ ገና ስትጀምር ዳዴን
ሄዋን ከመጸነሷ ከጅምር ላየ ስቃዩዋን
ህልቆ መሳፍርት የሌለው የመስዋዕትነት ድርሻዋን
ቆም በማለት አጢነን ከዳኘን በህሊናችን
ከአዳም ጋር ሲነጻጸር ብዙ ዕጥፍ ጀግና ናት ሄዋን !
ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ
ከምጥ ጭንቀት ፈቀቅ ባለ
ቀናት ሳምንታትን ተሻግሮ ወራት ሊያስጨንቅ የማለ
ያዳም ዘር ሊያዉቀው ሚገባ ለካስ በጽንስ ወቅት የባሰ አለ!
ወደእናትነት ጉዞ ስትቀላቀል ትግሉን
ብታዉቀዉም ሚያስከፍላትን
ህይወቷን አንዱን ያላትን
ድል ብትሆን የማትተካዉን
ግን አትሸሸዉም ዕሳቱን
የጦርነት ወላፈኑን
ጽንሱዋን የማርጋት ፍልሚያውን
ያብራኳን ክፋይ የማምጣቱን!
ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ
ከምጥ ጭንቀት ፈቀቅ ባለ
ቀናት ሳምንታትን ተሻግሮ ወራት ሊያስጨንቅ የማለ
ያዳም ዘር ሊያዉቀው ሚገባ ለካስ በጽንስ ወቅት የባሰ አለ!
ቆሜ ከጎኗ ከሄዋን ስላወቅሁ የማላዉቀዉን
ከኖርኩባቸው ዘመናት ልዩ ነው ለኔ ይህ ሰሞን
የመስዋዕትነት ድርሻዋን ሄዋኔ ስላሳየችኝ
የእናትነት ፍቅር አበሳን ተረዳሁ መጠን ግዝቨቱን
የረዥም ጉዞ ስቃይዋን በጽንሷ ጅምር አየሁኝ
በሷ ስቃይ ዉስጥ ደግሞ እናቴን ይበልጥ አወቅሁኝ!
ነጋሪቱ ይጎሰም ዘንድ አሁን አታሞ የታለ ?
የዘጠኝ ወር ስቃይ ዕምባ የሃሴት ጎርፍ ሆኖ መጣ በጉንጫችን ተንፏለለ
አይኗን በአይኗ – – – አይኔን ባይኔ የጨቅላ ድምጽ ተከተለ!
ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ
ከምጥ ጭንቀት ፈቀቅ ባለ
ቀናት ሳምንታትን ተሻግሮ ወራት ሊያስጨንቅ የማለ
የአዳምዘር ሊያዉቀው ሚገባ ለካስ በጽንስ ወቅት የባሰ አለ!
___________________________//______________________________
መታሰቢያነቱ ለኔዋ ሄዋን ለዕናቴና ለናቶች ሁሉ
ተጻፈ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም.
በሃብታሙ ደሃ
ሱንድስቫል ሆስፒታል
ስዊድን